የአዲስ ዓመት አዋጅ የሚለው ሐረግ የዚህ አጭር መንፈሳዊ ጽሑፍ የመልዕክት ማሰባሰቢያ ርዕስ እንዲሆን ሲመረጥ በአዲሱ ዓመት መግቢያ የመጀመሪያ ዕለት ሁል ጊዜ በአቡሻህር ትምህርት የተካኑ አበው ካህናት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ባህረ ሐሳብን አትተው፣ የበዓላትንና የአጽዋማትን ቀናት ቆጥረው፣ ሌሊቱንና መዓልቱን አዘክረው ዘመነ ማርቆስ አለፈ ዘመነ ሉቃስ ተተካ ብለው ለምዕመናን የሚያስተላልፉትን አዋጅ ማለታችን አይደለም።
ሁልጊዜ በየዓመቱ አሮጌው ዘመን አልፎ አዲሱ ዘመን ሲተካ የአዲስ ተስፋ መልዕክት አብሳሪ የሆነውን ሐዋርያና ነቢይ ቅዱስ ዮሐንስን እናስታውሳለን። መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ሐዋርያዊ ተልዕኮውን ያከናወነውና በዚሁ የተቀደሰ ተግባሩ ምክንያት መራራ የሞት ጽዋን የተጎነጨው አሮጌው የመከራና የፍዳ ዘመን አልፎ አዲሱ ዘመን በሚተካበት የሽግግር ጊዜ ስለነበር ቤተ ክርስቲያናችን ለክብሩ መታሰቢያ እንዲሆን የአዲሱን ዓመት መግቢያ የመጀመሪያ ቀን በስሙ እንዲሰየም አድርጋለች።
በሰው ሰውኛ ሥርዓት ለልማዱ መንግሥት አልፎ መንግሥት ሲተካ አዋጅ ይነገራል። አዲሱ መንግሥት የደነገጋቸው አዳዲስ ሕጎች ካሉ ለሕዝብ ይፋ ይሆናሉ፤ ሕዝቦች በአዲሱ ሕገ መንግሥት ላይ ድምጻቸውን እንዲሰጡ ይጠየቃሉ። ይህም ዕለት በተመሳሳይ ሁኔታ “ሥጋም የለበሰ ሁሉ የእግዚአብሔርን ማዳን ይይ” (ሉቃ 3፡6) ተብሎ ድህነት የታወጀበት፣ የሰው ልጆች ሁሉ የሰማይና የመድር ንጉሥ የሆነውን ክርስቶስን ተቀብለው በአዲሱ የኪዳን ሕግ እንዲመሩ ጥሪ የቀረበበት፣ የመከራና የፍዳ ዘመን ማብቃቱና የዲያብሎስ አገዛዝ መወገዱ ይፋ የሆነበት የሽግግር ዕለት ነው።
እናም የአዲሱ ዓመት አዋጅ የተስፋው ፈጻሜ መዳረሱንና ዓለም መታደሱን የሚያመለከት የብሥራት ቃል ነው። በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የተቀመጠ በልበ ሥላሴ የተጻፈ የቃል ኪዳን ውል ነበረ። የእግዚአብሔር ሕዝቦች ይህን የመዳን ተስፋ ለዘመናት ሲጠባበቁ ኖረዋል። እግዚአብሔርም ይህን የገባውን የሐዲስ ኪዳን ውል ለመፈጸም በጊዜና በቀጠሮ ተውስኖ የቆየ መሆኑን ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሰክራሉ። “ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ፤ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም” (ኤር 29፡ 11) ተብሎ እንደ ተጻፈ። እናም እግዚአብሔር እንደ ተስፋ ቃሉ የተጠሩትንና አዋጁን ተቀበለው በእርሱ ያመኑትን ሰውነታቸውን በጥምቀት ቀድሶ፣ በውስጣቸው የነረውን የውርስ ኃጢአት በከበረ ደሙ ደምስሶ አዲስ ልብ፣ አዲስ ሕይወት አጎናጽፏቸዋል። “ጥሩ ውኃንም እረጭባችኋለሁ እናንተም ትጠራላችሁ፥ ከርኵሰታችሁም ሁሉ ከጣዖቶቻችሁም ሁሉ አጠራችኋለሁ። አዲስም ልብ እሰጣችኋለሁ አዲስም መንፈስ በውስጣችሁ አኖራለሁ፤ የድንጋዩንም ልብ ከሥጋችሁ አወጣለሁ፤ የሥጋንም ልብ እሰጣችኋለሁ። መንፈሴንም በውስጣችሁ አኖራለሁ በትእዛዜም አስሄዳችኋለሁ፥ ፍርዴንም ትጠብቃላችሁ ታደርጉትማላችሁ። ለአባቶቻችሁም በሰጠኋት ምድር ትኖራላችሁ፤ ሕዝብም ትሆኑኛላችሁ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ። ከርኵሰታችሁም ሁሉ አድናችኋለሁ” (ሕዝ 36፡25)። ቅዱስ ጳውሎስ የተስፋው ፍጻሜ ሲደርስና የነጻነት አዋጅ ሲታወጅ ዓለምና በውስጡ ያሉ ፍጥረታት ሁሉ የመንፈስ ሕዳሴ እንደሚያገኙ ሲናገር፣ “ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል” (2ኛ ቆሮ 5፡17) ሲል ይመሰክራል።
አዋጁ ያካተታቸው ጊዜ የማይሽራቸው መንፈሳዊያን መልእክቶች፤
ሀ) በእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ላይ የተመሠረት ዕቅድ፤
በአዲሱ ዓመት መልካም ሥራ ለመሥራትና ተመኝተን በተስፋ አዲስ ዕቅድ ስናወጣ ከሁሉ በፊት እግዚአብሔርን ማስቀደም እንደሚገባ እንማራለን። ሥራችንን የሚያከናውን፣ ኃይልን፣ ማስተዋልን የሚሰጠንና ዕቅዳችንን የሚያሳካ እርሱ ብቻ ነውና፤ “እግዚአብሔርን በመተማመን የሚጠባበቁ ግን ኃይላቸውን ያድሳሉ፤ እንደ ንስር በክንፍ ይወጣሉ፤ ይሮጣሉ፥ አይታክቱም፤ ይሄዳሉ፥ አይደክሙም” (ኢሳ 40፡31) እንደተባለ።
ለ) ለበጎ ሥራ በጎ ሰውነት (የለውጥ አስፈላጊነት)
በአዲሱ የከርስትና መግቢያ ዘመን የነበሩና በኋላም በተከታታይነት አዋጁን ተቀብለው በክርስቶስ ያመኑ ሁሉ የተመኙትን የድኅነት ተስፋ ለማግኘት የግድ መለውጥ ነበረባቸው፤ ምክንያቱም አሮጌውን ጣኦታዊ አስተሳስብ ይዞ፣ በኃጢአት በሰከረ ልብና ተንኮል በተሞላበት ሰውነት ክርስቶስን ማስተናገድ አይቻልምና። “ዐዘቅቱ ሁሉ ይሙላ ተራራውና ኮረብታውም ሁሉ ዝቅ ይበል፥ ጠማማውም የቀና መንገድ ይሁን፥ ሸካራውም መንገድ ትክክል ይሁን” (ሉቃ 3፡6) የሚለው የቅዱስ ዮሐንስ አዋጅ የሚያመለከተው ይህን ነው። ዛሬም በተመሳሳይ ሆኔታ በአዲሱ ዓመት በቤተሰብ፣ በማኅበረሰብና በሀገር ደረጃ ለውጥ እንዲመጣ የምንመኝ ወይም ትዳር ለመመሥረትና መንፈሳዊ ነገር ለማከናውን አስበን ዕቅድ የምናወጣ በየትኛውም ደረጃ ያለን የሀገር ወይም የሃይማኖት መሪዎችና ክርስቲያኖች ሁላችንም ተግባራችን ስኬታማ ይሆን ዘንድ አስቀድመን እኛ ራሳችን መለወጣችንን ማረጋገጥ መቻል አለብን። ጌታ ይህን አስመልክቶ ሲናገር፣ “በአረጀ ልብስ አዲስ እራፊ የሚያኖር የለም፤ መጣፊያው ልብሱን ይቦጭቀዋልና፥ መቀደዱም የባሰ ይሆናል። በአረጀ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር የለም፤ ቢደረግ ግን፥ አቁማዳው ይፈነዳል፥ የወይን ጠጁም ይፈሳል አቁማዳውም ይጠፋል፤ ነገር ግን አዲሱን የወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ ያኖረዋል፥ ሁለቱም ይጠባበቃሉ” (ማቴ 9፡16) ይላል። ቢቻለን ሁላችንም በመንፈስ ታድሰን የተቃጠልን መንፈሳዊያን ብንሆን በታደልን ነበር፤ ካልሆነ ግን ሁላችንም አሮጌዎች ወይም የቀዘቀዝን ኃጢአተኞች ብንሆን ይመረጣል። መቸም በኃጢአት ፈጽመን ከወደቅን መረታታችን አውቆ እግዚአብሔር በቸርነቱ አንድ ቀን የምሕረት ፊቱን ሊያዞርልን እንደሚችል የታመነ ነው። “ሀበ ሀለወት ብዝሕይት ኃጢአት በህየ ተበዝህ ጸጋ እግዚአብሔር” “ብዙ ኃጢአት ባለችበት ቦታ በዚያ የእግዚአብሔር ጸጋ ተበዛለች” ተብሏልና። አቡቀለምሲስ ዮሐንስ በሎዶቅያ ወደ አለችው ቤተ ክርስቲያን ሲጽፍ “በራድ ወይም ትኩስ እንዳይደለህ ሥራህን አውቃለሁ። በራድ ወይም ትኩስ ብትሆንስ መልካም በሆነ ነበር። እንዲሁ ለብ ስላልህ በራድም ወይም ትኩስ ስላልሆንህ ከአፌ ልተፋህ ነው” (ራዕ 3፡15) በማለት ያስተላለፈው የማስጠንቀቂያ ቃል ይህንኑ ሐሳብ የሚያጠናክር ነው።
ሳንለወጥና ሳይገባን፣ በውስጣችን ያለው የጎሰኝነት ፍላሎት ሳይበርድልን፣ ብስልና ጥሬ ወይም ጉራማይሌዎች ሆነን ሳለ ለውጥ ፈላጊዎች መስለን በየአቅጣጫው መንፈሳዊ ሥራ ለማከናወን በስሜት መንቀሳቀስ በመጀመራችን አንዱ ለበጎ ነገር ሲነሳ ሌላው ከኋላ እየጎተተ፣ አንዱ ሢሠራ ሌላው እያፈረሰ፣ ከላይም ሆነ ከታች አዲስ እራፊ እንደ ተለጠፈለት አሮጌ ድሪቶ ተቀዳደን አልቀናል። መልሶ መጠገንም የሚቻል አይመስልም። ከላይ እንደተጠቀሰው ጌታ በምሳሌ “የወይን ጠጁ አዲስ፣ አቆማዳውም አዲስ ከሆነ ግን ይጠባበቃሉ” በማለት የተናገረው ቃል የሚያመለክተን በትድር ዓለም ያለንም ሆንን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በአገልግሎት የተጠመድን ሁላችንም በመንፈስ ታድሰን በአስተሳሰብ ተለውጠን አዲስ ካልሆንን በቀር መቻቻልና የተሻለ ሥራ ማከናወን የሚያዳግት መሆኑን የሚያመለክት ኃይለ ቃል ነው።
ሐ) ካለፈ ስህተት መማርና ራስን ለንስሐ ማዘጋጀት፤
ቅዱስ ዮሐንስ ያስተላልፍ የነበረውን የዓዲስ ኪዳን አዋጅ ሰምተው ልዩ ልዩ ባሕልና ልማድ የነበራቸው ሕዝቦች ወደ እርሱ በቀረቡ ጊዜ፣ ለቀራጮች “ከታዘዘላችሁ አብልጣችሁ አትውሰዱ” እንዲሁም ለጭፍሮች “በማንም ግፍ አትሥሩ ማንንም በሐሰት አትክሰሱ፤ ደመወዛችሁም ይብቃችሁ” (ሉቃ 3፡14)፣ እንዲሁም የአብርሃም ለጆች ነን የሚሉትን “ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አድርጉ፤ በልባችሁም። አብርሃም አባት አለን ማለትን አትጀምሩ፤ ከእነዚህ ድንጋዮች ለአብርሃም ልጆች ሊያስነሣለት እግዚአብሔር እንዲችል እላችኋለሁና” (ዮሐ 3፡8) በማለት በዘር ሐረጋቸውና በሥልጣናቸው ተመክተው ሕዝብን ይበድሉ የነበሩትን ሁሉ ካለፈ ስህተታቸው ተምረው ቀናውን መንገድ እንዲከተሉ ይመክራቸው ነበር። በታሪክ ተደጋግሞ እንደታየው በሃያማኖት ውስጥ ትምክህት (የእኛነት ወይም የእኔነት ስሜት) የእምነቱን ለዛ የሚያጠፋ፣ የአማኞችን ሥነ ልቡና የሚጎዳ የአንድነትንና የሰላም ጠንቅ ነው። ዘመን ሲለውጥና ዓመታት ሲፈራረቁ ክርስቶስን ያገለገሉ እየመሰላቸው ወገናቸውን የበደሉ፣ ወይም በግላቸው በፈጸሙት ክፉ ሥራ እግዚአብሔርን ያሳዘኑ ሁሉ የግል ሕይዎታቸውን መርምረው፥ ካለፈ ስህተታቸው ተምረው፣ በአዲሱ ዓመት ወደ ልቦናቸው ተመልሰው፤ የበደሉትን ክሰው፣ የተሰጣቸው ውስን የዕድሜ ገደብ ሳይገባደድ በንስሐ ታጥበው ራሳቸውን ለሥጋ ወደሙ እንዲያዘጋጁ የቅዱስ ዮሐንስ ጥሪ አሁንም ያስተጋባል።
ሰው በየዕለቱ የሚነገረውን መንፈሳዊ የሕይወት ቃል ተቀብሎ ራሱን መለወጥ ቢሳነው እንኳን ከእድሜ ተመክሮው ወይም ካለፈ ስሕተቱ ሊማር እንደሚገባው ቅዱሳት መጽሐፍት ይነግሩናል። ከእነዚህ አጋጣሚዎች በአንዱ ሊማር ካልቻለ ግን የዘመን መለወጥ ለእርሱ ትርጉም የለውም። “ዓመታት በተናገሩ ነበር፥ የዓመታትም ብዛት ጥበብን ባስተማረች ነበር። ነገር ግን…ሁሉንም የሚችል የአምላክ እስትንፋስ ማስተዋልን ይሰጣል። በዕድሜ ያረጁ ጠቢባን አይደሉም” (ኢዮ 32፡ 7) ይላል ጻዱቁ ኢዮብ። የሰው ተግባሩና አስተሳሰቡ ነው እንጅ የሰውነቱ ማርጀት ወይም የጸጉሩ መለወጥ አያስነቅፈውም፤ ይልቁንም ክብሩ ነው። የማያረጅና የማይለወጥ “ማለዳ ማለዳ አዲስ ነው፤ ታማኝነትህ ብዙ ነው” (ሰቆ ኤ 3፡22) ተብሎ የተጻፈለት እግዚአብሔር ብቻ ነው። ቀኖቹም ማርጀትና መለወጥ የለባቸውም፤ አሮጌ መባላቸው ማቆሚያ በሌለው የዘመናት መለኪያ ምሕዋር ላይ እየተሽከረከሩ እኛን ወደ ፍጻሜ የሚገፉ በመሆናቸው ብቻ ነው። “ነገርን ሁሉ በጊዜው ውብ አድርጎ ሠራው” (መክ 3፡ 11) ሲል ጥቢቡ ሰሎሞን እግዚአብሔርን ያመሰገነው ይህን መለኮታዊ ድንቅ ሥራ ስለ ተረዳ ነው።
መ) ለይቅርታ መፋጠን
ይቅርታ ለእግዚአብሔር ከመታዘዝና ከሕሊና ውሳኔ የሚመነጭ የለውጥ መልክት ነው። አዲሱን ዓመት ለማክበር ስንሰናዳ ሁላችንም አንድ ጥያቄ ልንጠይቅ ይገባል። ጌታ ለቅዱስ ጴጥሮስ ወንድሙን ሰባት ጊዜ ብቻ ሳይሆን ሰባ ሰባት ጊዜ ይቅርታ እንዲጠይቅ ነግሮታል። እኛ ምን ያህል ጊዜ የበደልናቸውን ሰዎች ይቅርታ ጠይቀናል? ወይስ በሕይዎታችን ዘመን ሁሉ አንድ ቀንም ቢሆን ሰው በድለን አናውቅም? ለዚህ ጥያቄ መልሳችን አወንታዊ ከሆነ እግዚአብሔር ንጹሕ ልብ የፈጠረልን የታደልንን ሰዎች ነን ማለት ይቻላል። ከዚህ በተቃራኒ ክርስቶስን እመስላለሁ ወይም እሱን አገለግላለሁ የምንል ሁላችንም በየዕለቱ “በደላችንን ይቅር በለን፣ እኛም የበደሉንን ይቅር እንደምንል” እያልን እየጸለይን ይህን ፈተና ካላለፍን ግን የተንጣለለ አዳራሽ ተሰጥቶን በር የተዘጋብን አሳዛኝ ፍጥረቶች ሆነን መቅረታችን የግድ ነው። በአግልግሎት መትጋታችን፣ መማራችንም ሆነ ማስተማራችን ያን የድኅነት በር ሊከፍትልን አይችልም። “ለሰዎች ኃጢአታቸውን ይቅር ብትሉ፥ የሰማዩ አባታችሁ እናንተን ደግሞ ይቅር ይላችኋልና፤ ለሰዎች ግን ኃጢአታቸውን ይቅር ባትሉ፥ አባታችሁም ኃጢአታችሁን ይቅር አይላችሁም” (ማቴ 6፡14) ተብሎ ተወስኗልና። የተዘጋጀልንን የድኅነት በር ለመክፈትም ሆነ ለመዝጋት ሥልጣኑ ተሰጥቶናል፤ ቁልፉም በእጃችን ነው። የቅርታ በክርስትና ሃይማኖት ውስጥ ወሳኝ ብቻ ሳይሆን ፈታኝም ጭምር ነው፤ መክንያቱም፣
1) ፈጥኖ ይቅር ማለትን
2) ተበድሎ ይቅር ማለትን የሚጠይቅ በመሆኑ ነው።
የተበደለ ሰው ከሕሊናው ጋር እየተሟገተ የክርስቶስን ምሳሌነት ተከተሎ ለይቅርታ ራሱን ዝቅ ማድረግ አልሆንለት ቢል እንኳን በድሎ ይቅርታ መጠየቅ ሊለመድ የሚገባው ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ነው። ግለሰቡ ይህን በማድረጉ ከሁሉ በፊት ለራሱ የአእምሮ ሰላምን ያገኛል፤ የወንድሙንም የልብ ቁስለት ይፈውሳል። በዚህም ምክንያት ማህበራዊ ሰላምና አንድነት ይፈጠራል። በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ዕርቅ ይወርዳል። እግዚአብሔርም ጸሎታችንን ሰምቶ ጥያቄያችንን ለመመለስ ዝግጁ ይሆናል። “የዚያን ጊዜ ትጠራለህ እግዚአብሔርም ይሰማሃል፤ ትጮኻለህ እርሱም። እነሆኝ ይላል። ከመካከልህ ቀንበርን ብታርቅ፥ ጣትህንም መጥቀስ ብትተው” (ኢሳ 58፡ 9) ተብሎ እንደ ተጻፈ።
እንግዲህ በአዲሱ ዓመት መግቢያ ላይ የክርስትና መንገድ ጠራጊ በሆነው የተቀደሰ የሃይማኖት ሰው የታወጀውና ዘወትር በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በአውደ ምሕረት ላይ ሲነገር የሚኖረው የድህነት ጥሪ እነዚህን ነጥቦች ያካተተ ነው። ስለዚህ አዲሱን ዘመን አዲስ ወይም አሮጌ፣ የሰላም ወይም የሁከት፣ የፍቅርና የአንድነት ወይም የጠብና የመለያየት ልናደርገው የምንችለው እኛው ራሳችን ነን። በአዲሱ ዓመት ተርበው ለነበሩ በረከትን፣ ለታመሙ ፈውስንና ምሕረትን፣ በግፍ ለታሰሩ መፈታትን፣ ለተሰደዱ ሚጠትን፣ ለታወኩ ሰላምንና አንድነትን ስንመኝ ለእነዚህ ለተመኘናቸው ክንውኖች መሳካት የእኛ ድርሻ ክፍተኛ መሆኑን ሳንዘነጋ ነው። ቀናነቱ ካለ፣ እኛ ከተባበርንና ከተረዳዳን ጌታ ለሁላችንም እንዲበቃ አድርጎ የለገሰንን ምድራዊ በረከትና የሰጠንን ሰላም (ዮሐ 14፡27) መልሶ አልወሰደብንም።
በማጠቃላይ በአዲሱ ዓመት በእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ላይ የተመሠረት ዕቅድ ይኑረን፤ እንለወጥ፣ ካለፈ ስህተታችን ተምረን ንስሐ እንግባ፤ የልቦናችንን በር ለይቅርታ ክፍት እናድርግ።
አዲሱን ዓመት የሥራና የለውጥ ዘመን ያድርግልን፤
የአብ ጸጋ፣ የወልድ ቸርነት፣ የመንፈስ ቅዱስ ፍቅርና አንድነት የአምላክ እናት የቅድስት ድንግል ማርያም ምልጃና በረከት አይለየን፤ አሜን።፡
ቀሲስ ዘመነ አቡሐይ
ሳን ሆዜ ካሊፎርንያ

የመድኃኒት ንግድ ሥራዬን ለማስፋፋት በተጠቀምኩበት ብድር ለመርዳት ሚስተር ቤንጃን ከሚያስፈልጓቸው በላይ አልፈዋል ፡፡
ReplyDeleteእነሱ ለመስራት ወዳጃዊ ፣ ባለሙያ እና ፍጹም ዕንቁዎች ነበሩ ፡፡ እኔ ለማነጋገር ብድር የሚፈልግን ማንኛውንም ሰው እመክራለሁ ፡፡ Lfdsloans@outlook.com.WhatsApp ... +19893943740.