በክርስትና ሃይማኖት የአምልኮት ክንዋኔ ሂደት ብዙውን መንፈሳዊ አገልግሎት የሚሸፍኑት ካህናት ቢሆኑም የምዕመናኑም ድርሻ በቀላሉ የሚገመት አይደለም። እንዲያውም የአንድ መንፈሳዊ አገልግሎት ስኬታማነት የሚለካው በካህናቱ ብቃትና በምዕመናኑ የነቃ ተሳትፎ ነው። በአሁኑ ዘመን በብዙ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ የሚስተዋለው ችግር የካህናት ቁጥር ማነስ ሳይሆን የብቃት ጉዳይ ነው። ይህ ችግር በእኛ ቤተ ክርስቲያን በእጅጉ ጎልቶ ይታያል። ይሁን እንጅ ምዕመናን ከአግልጋዮች የብቃት ማነስ ጋር በተያያዘ መልኩ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በየጊዜው የሚከሰቱትን መንፈሳዊና ማኅበራዊ ችግሮች ደጋግሞን እያነሳን ከማዘን ይልቅ ተስፋ ሳንቆርጥ ለለውጥ ራሳችንን አዘጋጅተን የድርሻችንን ብናበረክት የቤተ ክርስቲያንን ትንሣኤ ልናፋጥን እንደምንችል የታመነ ነው። ይህን ካልን ዘንድ የቤተ ክርስቲያንን ትንሣኤ ሊያፋጥን የሚችል ምን ዓይነት አገልግሎት ልናበረክት እንችላለን ብሎ መጠየቅ የግድ ይሆናል።
ሀ) የቤተ ክርስቲያን አባቶችን ሕይወት ማነጽ፤
1) አብሮ በመሥራትና የሕይወታቸው አጋር በመሆን፤
በክርስቶስ ቤት መንፈሳዊ እንክብካቤና ጥበቃ እየተደረገላቸው ቃሉን ተመግበው መንፈሳዊ ፍሬን እንዲያፈሩ የሚጠበቅባቸው ምዕመናን በወይን ሐረግ ተመስለዋል። የወይን ሐረጉ መልካምና ተወዳጅ ፍሬ እንዲያፈራ ከተፈለገ ለወይን ሐረጉ ድጋፍ የሚሰጥ ምሰሶ እንዲኖርና እንዲሁም ሐረጉ ከውይን ግንዱ ጋራ እንዳይነጣጠል መጠበቅ ያስፈልጋል። በዚህ ምሳሌ የወይን ሐረግ የተባሉ ምዕመናን፣ የወይን ግንድ የተባለ ጌታ ሲሆን፣ እንዲሁም ድጋፍ ሰጭ ምሰሶ የተባሉ ካህናት ናቸው። የወይኑን ሐረግ የሚሸከም ምሰሶ ከሌለ ወይኑ በራሱ ሊቆምና ተፈላጊውን ፍሬ ሊያስገኝ እንደማይችል ሁሉ በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ያለ ካህናት ድጋፍ ምዕመናን በራሳቸው ትጋትና ጸሎት የእግዚአብሔርን መንግሥት መውረስ ይሳናቸዋል። እናም ከምንመኘው የዕድገት ደረጃ ለመድረስና መንፈሳዊ ፍሬን ለማፍራት ምሰሶው እንዳይንገዳገድ ማጠናከር ወይም መንፈሳዊ ዝለትና ድካም ያጋጠማቸውን ካህናት በመፈሳዊ ዓላማ እንዲጸኑ ለእነርሱ ድጋፍ ማድረግ ከምዕመናን ይጠበቃል።
ራሳቸውን ለእግዚአብሔር የሰጡ አባቶች የመንገዳገድ አዝማሚያ ቢያሳዩ እነሱን ማስተማርና መምከር ለምዕመናን አዳጋች መስሎ ሊታይ ይችል ሆናል። በእርግጥም ከባድ ነው። ነገር ግን ከካህናቱ ጋር በፍቅር አንድ ሆነን አብረን ከሠራንና የሕይወታቸው አጋር ሆነን ከተገኘን፣ ችግሮች ሲከሰቱ ለማሳሰብና የአባቶችን ልብ በፍቅር ለማሸነፍ ዕድል እናገኛለን። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በፊልጵስዩስ ምዕመናን ታዛዥነት ልቡ ተነክቶ እንዲህ ብሏል።
“ከፊተኛው ቀን እስከ ዛሬ ድረስ ወንጌልን በመስበክ አብራችሁ ስለ ሠራችሁ፥ ባሰብኋችሁ ጊዜ ሁሉ አምላኬን አመሰግናለሁ። በእናንተ መልካምን ሥራ የጀመረው እስከ ኢየሱስ ክርስቶስ ቀን ድረስ እንዲፈጽመው ይህን ተረድቼአለሁና፤ በእስራቴም ወንጌልንም መመከቻና መጽኛ በማድረግ ሁላችሁ ከእኔ ጋር በጸጋ ተካፋዮች ስለ ሆናችሁ፥ በልቤ ትኖራላችሁና ስለ ሁላችሁ ይህን ላስብ ይገባኛል። በክርስቶስ ኢየሱስ ፍቅር ሁላችሁን እንዴት እንድናፍቃችሁ እግዚአብሔር ምስክሬ ነውና። ለእግዚአብሔርም ክብርና ምስጋና ከኢየሱስ ክርስቶስ የሚገኝ የጽድቅ ፍሬ ሞልቶባችሁ፥ ለክርስቶስ ቀን ተዘጋጅታችሁ ቅኖችና አለ ነውር እንድትሆኑ የሚሻለውን ነገር ፈትናችሁ ትወዱ ዘንድ፥ ፍቅራችሁ በእውቀትና በማስተዋል ሁሉ ከፊት ይልቅ እያደገ እንዲበዛ ይህን እጸልያለሁ”(ፊልጵ 1፡ 3-12)።
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እነዚህ ምዕመናን በችግር ጊዜ የመከራው ተካፋይ በመሆን ተአማኝነታቸውን ስለ አረጋገጡለት “በልቤ ትኖራላችሁ” አለ። ካህናት በጎ ሥራ ሢሠሩ በሥራቸው የምንደሰተውን ያህል ጥፋት ሲፈጽሙም ቅሬታችንን መግልጽ የምንችለው በችግር ቀናት አጋሮች ሆነን ስንገኝና ለአገልግሎቱ መፋጠን አብረን በሥራ ስንሰለፍ ነው እንጅ ከሩቅ ሆነን ጥፋቶቹን እያጎላን በመተቸት አይደለም። የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ አገልግሎት ከፕሮቴስታንት ጋር በብዙ መንገድ ይለያያል። በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የክህነት አገልግሎት ልዩ ነው፤ የአገልግሎት መስጫ ቦታውም የተልየና የተቀደሰ ነው። ስለዚህ ምዕመናን ከካህናት ጋር ተቀራርበው በመሥራት አጋርነታቸውን ማሳየት አለባቸው ሲባል ቦታችንንና የሥራ ድርሻችንን ለይተን አውቀን፣ ከጣልቃ ገብነት ተጠንቅቀን፣ ከእርግማን ርቀን ለአገልግሎቱ ስኬታማነት መተባበር አለብን ማለታችን ነው። በዚህ መንገድ የድርሻችንን ጠብቀን የምናበረክተው አገልግሎት በኑሯችንና በሕይዎታችን አምላካዊ በረከትን፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሰላምን፣ በካህናትና በምዕመናን መካከል ፍቅርንና አንድነትን ያመጣል። ካህናት በአገልግሎታቸው ደስተኞች እንዲሆኑና ለበለጠ ሥራ እንዲተጉ ይረዳል።
2) በጸሎት ማገዝ፤
የቤተ ክርስቲያን አባቶች ሌሊት በማኅሌትና በሰዓታት፣ ቀን በኪዳንና በቅዳሴ ስለ አገር አንድነት፣ ስለ ሕዝብ ደኅንነትና በጠቅላላው ስለ ዓለም ሁሉ እንደሚጸልዩ፣ ምዕመናንም በድርሻቸው እግዚአብሔር ለካህናቱ ብርታትን እንዲሰጣቸውና አገልግሎታቸውንም ወዶ እንዲቀበልላቸው መጸለይ ይገባል። ለብዙ መንፈሳዊ ነገሮች አብነት የሚሆነን ቅዱስ ጳውሎስ በአካል እስከ ሦስተኛው ሰማይ ድረስ የተነጠቀ፣ የመንፈስ ልዕልና የተሰጠው ታላቅ ሐዋርያ ሆኖ ሳለ ስለ ፍቅር ሲል እግዚአብሔር የቃሉን ደጅ ለአገልጋዮች እንዲከፍትላቸው ማለትም ምሥጢሩን እንዲገልጽላቸውና (ቆላ 4፡3)፣ ይልቁንም ደግሞ የካህናቱ አገልግሎታቸው ክርስቲይኖችን የሚያስደስት እንዲሆን ምዕመናን በጸሎት ያስቧቸው ዘንድ የአደራ መልእክቱን ሲያስተላልፍ እናስተውላለን (ሮሜ 15፡31)። ቅዱስ ጳውሎስ ይህን መልእክት ያስተላለፈው “የደስታየ አክሊል” ለሚላቸውና ለሚወዳቸው ምዕመናን ነው። አንዱ ለሌላው መጸለይ የፍቅርና የአንድነት ምልክት ነው። ለሃያማኖት አባቶች መጸለይ ማለት ለቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት መጸለይ ማለት ነው። በግብፅና በሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ጳጳሳት ለዓመታዊ የቤተ ክርስቲያን ጉባዔ ለሲኖዶስ በሚሰበሰቡበት በዚህ ወራት መንፈስ ቅዱስ አብሯቸው እንዲሠራና የቤተ ክርስቲያንን ቀጣይ ጉዞ እንዲቃና ምዕመናን በውጭ ሆነው በጸሎት ይተጋሉ።
አንድ አገልጋይ ካህን ሰው ነው እንጅ መልአክ አይደለም፤ የእግዚአብሔር መንፈስ ካልተዋሐደው በቀር በራሱ ፍጹም ሊሆን አይችልም። እናም የካህናትን ደካማ ሕይዎት ማስተካከልና የቤተ ክርስቲያንን ችግር መፍታት የሚቻለው በመንፈስ ቅዱስ አጋዥነት በጸሎትና በምክክር ነው እንጅ ጥቃቅን ስህተቶችን አጉልቶ እያወጡ ግለሰቡ እንዲሸማቀቅና ከሃይማኖት እንዲርቅ በማድረግ አይደለም። ሃይማኖቱን የሚያከብር ወንድሙን የሚወድ አማኝ የሌላውን ሰው ገመና አውጥቶ ለመናገር መንፈሱ ይጭነቃል፤ ከነቀፌታ በፊት ምክክርን ይመርጣል።
ለ) ለመንፈሳዊ ዕድገት ያለ መታከት መሥራት፤
የወይን ሐረግ ተሸካሚ ምሰሶው ጽኑና ብርቱ ሆኖ ነገር ግን የወይን ሐረጉ ፍሬ መስጠት ቢሳነው የራሱ ድክመት ነውና ፍሬ የማይሰጥ የመከነ ወይን ተብሎ ለመርገም ተላልፎ ይሰጣል፤ “አጥሩን እነቅላለሁ፥ ለማሰማርያም ይሆናል፤ ቅጥሩንም አፈርሳለሁ፥ ለመራገጫም ይሆናል፤ ባድማ አደርገዋለሁ” (ኢሳ 5፡ 5) ተብሎ ተነግሮበታል። ካህናት ድጋፍ ሰጭ አስተማሪዎች ናቸው እንጅ የሰውን ሕይወት በቀጥታ የመለወጥ ሥልጣን የላቸውም። በተሰጠው መልካም የመዳን ዕድል ተጠቅሞ ራሱን መለወጥ የእያንዳንዱ ምዕመን ድርሻ ነው። “በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ” (ፊልጵ 2፡12) ሲል ቅዱስ ጳውሎስ እንደተናገረ። በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ድኅነት ወይም መንፈሳዊ ዕድገት በሥራ እንጅ በማመን ብቻ ይሚገኝ አይደለም። እናም ቤተ ክርስቲያን የሚለው ቃል በቀጥተኛ ትርጉሙ የእኛን ሕይወት የሚወክል እንደመሆኑ የቤተ ክርስቲያን ዕድገት በእኛ የሕይዎት ለውጥ ላይ የሚወሰን ይሆናል። ምዕመናን በሕይወታቸው የሚያሳዩት መንፈሳዊ ለውጥ የቤተ ክርስቲያንን ዕድገት ብቻ ሳይሆን የካህናቱንም አስተሳሰብ ይለውጣል። በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ እያለን በኑሯችንና በሕይወታችን ቤተ ክርስቲያንን እንዳናስነቅፍና እኛም ተለውጠን የበረከቱ ተካፋዮች እንድንሆን የሚከተሉትን መንፈሳዊ መርሆዎች ተከትለን መሥራት ይጠበቅብናል።
· ቃሉን በየዕለቱ መማርና ማንበብ፣
ኦርቶዶክሳዊያን ክርስትናን በልማድ ተቀብለን በልማድ የምንኖር ሳንሆን በየዕለቱ በማንበብና በመማር ለመንፈሳዊ ዕድገት ጥረት የምናደርግ፣ የሃይማኖታችንን ዶግማና ቀኖና ጠንቅቀን የምናውቅ፣ ለምንጥየቀው ሁሉ አጥጋቢ ምላሽ የምንሰጥ በአጠቃላይ የተሟላ መንፈሳዊ ትጥቅ ያለን የእምነት አርበኞች እንድንሆን ያስፈልጋል። “የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ልታጠፉ የምትችሉበትን የእምነትን ጋሻ አንሡ፤ የመዳንንም ራስ ቁር የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው” (ኤፌ 6፡ 16)። “ለሚጠይቁዋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ፥ ነገር ግን በየዋህነትና በፍርሃት ይሁን” 1 ጴጥ 3፡15)ተብሎ ተጽፎልናልና። መማራችንና በቃሉ ማደጋችን ትዕግስተኞችና አስተዋዮች፣ ለትችት የማንፋጠን እንድንሆን ይረዳናል። የ2000 ዓመታት ታሪክ ባላት በጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሆነን ማንም ከመሬት ተንስቶ ከአላዋቂዎችና ከጣኦት አምላኪዎች ተራ የሚፈርጀን የራሳችንን እምነት ለማወቅ ፍላጎት የሌለን ግዴለሾች ስለሆንን ነው። እንግዲያውስ የእግዚአብሔር መንግሥት በድካምና በጥረት እንጅ በግዴለሽነት አይወረስምና እንጠንቀቅ። በስንፍናችን ራሳችንንም ሆነ ቤተ ክርስቲያናችንን አናስነቅፍ።
· ከኃጢአት መታቀብ፣
መማርንና ማወቅን ተከትሎ የሚመጣው የመንፈሳዊ ዕድገት ደረጃ ከኃጢአት መታቀብ ነው። ብዙ ባወቅንና የቅዱሳንን ገድልና ሕይወት በተረዳን መጠን ራሳችንን ከኃጢአት ለመግታት ብርታት እናገኛለን። ትግሉ ከወንድማችን ጋራ መሆኑ ቀርቶ ከራሳችን ሥጋዊ ስሜት ጋር ይሆናል። ደረጃ በደረጃ እየተለወጥን ስለ ራሳችን ኃጢአት ማልቀስ እንጀምራለን። ቀስ በቀስ እየተለወጥን እግዚአብሔርን ወደ መምስለ ደረጃ እንሸጋገራለን፣ “የመለኮቱ ኃይል፥ በገዛ ክብሩና በበጎነቱ የጠራንን በማወቅ፥ ለሕይወትና እግዚአብሔርን ለመምሰል የሚሆነውን ነገር ሁሉ ስለ ሰጠን፥ በእግዚአብሔርና በጌታችን በኢየሱስ እውቀት ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ” (2ጴጥ 1፡3)።
· በጸሎተ ቅዳሴ ጊዜ የነቃ ተሳትፎ ማድግ፣
የመንፈስ ጥንካሬ የግል ጸሎትን በመለማመድ ይጀምራል። የግል ጸሎትን የተለማመደ ክርስቲያን ቁሞ ማስቀደስ አይከብደውም። በተለይም በቅዳሴ ጊዜ ተሰጥኦ መቀበል የአንድ ክርስቲያን መንፈሳዊ ተሳትፎና ትጋት የሚመዘንበት፣ የቤተ ክርስቲያንም ዕድገት የሚለካበት ሁለተኛው መንገድ ነው። ስለዚህ ኦርቶዶክሳዊን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ቆመው ተሰጥኦ በመቀበል በአገልግሎት ውስጥ መሳተፍ መንፈሳዊ ግዴታቸው መሆኑን እንዲያውቁና ለዚህ ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ ያስፈልጋል። አንድ በጋራ ጸሎት የሚሳተፍ አማኝ ቆሞ የሚያስቀድስበት ቋሚ ቦታ እንዲኖረውና፣ እንዲሁም የአምልኮት አገልግሎቱ የሚሰጠው በባዕድ ቋንቋ እስካልሆነ ድረስ ሌሎችን እየተከተለ የምስጋና ድምጹን በማሰማት የበረከቱ ተካፋይ እንዲሆን ያስፈልጋል። ተሰጥኦ መቀበል ቢያዳግተው እንኳን ድምጹን ከፍ አድርጎ “አ ሜ ን” ማለት መቻል አለበት።
· በልዩ ልዩ የአገልግሎት ዘርፎች መሳተፍ፣
ብዙዎቹ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባቶች በርካታ የሕይወት ዘመናቸውን ያሳለፉት እየተዳከመ የመጣውን የቤተ ክርስቲያናችን ነባር ትምህርት በቃል በማጥናትና ተተኪ ለማፍራት ሌሎችን በማስተማር ነው። እናም በዚህ በሰለጠነው ዓለም የዘመኑን የዕድገት ደረጃ ተከትሎ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጥና ሕዝበ ክርስቲያኑ በተዋሕዶ እምነት ጸንቶ እንዲኖር ለማድረግ ችሎታቸው በሚፈቅደው ሁሉ የአገልግሎቱ ድጋፍ ሰጭ የሆኑ ነገሮችን ሟሟላትና አባቶችን ማገዝ ከምዕመናን ይጠበቃል። ሁላችንም የተለያየ የአግልግሎት ድርሻ ያለን የአንድ አካል ልዩ ልዩ ብልቶች ነን (1 ቆሮ 12፡1)። ቅንነትና በጎነት ካለ ካህኑ አባቶቻችን ያቆዩልንን ሥርዓት (የሐዋ 6፡ 4)ተከትሎ የቤተ ክርስቲያን ራስ ቢሆን ምዕመናኑ እጅና እግር ሆነው ሊያገለግሉ ይችላሉ። በዚህም የተቀናጀ የአገልግሎት ሂደት ውስጥ መደጋገፍና መከባበር የመንፈሳዊነትና የብስለት መለኪያዎች ሆነው ይቀጥላሉ።
· ንስሐ መግባትና ሥጋውና ደሙን መቀበል፣
እስከ አሁን ድረስ የተዘረዘሩት አራቱ ነጥቦች እንደ ግለሰቡ ቀናነት በአንድ ጊዜ ወይም ደረጃ በደረጃ ሊፈጸሙ ይችላሉ። ሆኖም እነዚህ ነጥቦች ጸጋና በረከትን ካማሰጠት አልፎ በራሳቸው አማኙን ፍጹም ሊያደርጉት አይችሉም። እነዚህን ደረጃዎች ተከትሎ ሕዝብንና እግዚአብሔርን የሚያገለግል አንድ ምዕመን ከድካሙ ፍሬ እንዲጠቀምና ለሌሎችም አርያአና ምሳሌ እንዲሆን ንስሐ ገብቶ ሥጋና ደሙን መቀብል ይገባዋል። በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በብዙ የአግልግሎት ዘርፎች ተሳታፊ እየሆነ ነገር ግን ንስሐ የማይገባና ሥጋና ደሙን የማይቀበል ምዕመን ምሳሌነቱ ለሌሎች ምዕመናን የማይበጅ ብቻ ሳይሆን ቤተ ክርስቲያንንም ተራ የሲቪል ተቋም እያደረጋት ስለ ሆነ የቤተ ክርስቲያን አባቶች በዚህ ላይ ብርቱ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል። ከቅዱስ ጴጥሮስ ቀጥሎ የአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን 3ኛ ሊቀ ጳጳስ ሆኖ የተሾመው ቅዱስ አግናጥዮስ በፍላብያን ዘመን ለሰማዕትነት ወደ ሮም ይወሰድ በነበረበት ጊዜ ለክርስቲያኖች ባስተላለፈው መልዕክት ስለ ሥጋና ደሙ ሲጽፍ “ከሞት የምናመልጥበትና ሕያው ሆነን ከክርስቶስ ጋራ ለዘለዓለም አብረን የምኖርበት ፍቱን መድኃኒት” ብሎታል።
እንግዲህ በአጠቃላይ ቤተ ክርስቲያናችን ካህናትና ምዕመናን “በጸሎትህ አስበኝ” እየተባባሉ ሰምና ወርቅ ሆነው የሚሠሩባት፣ ምዕመናን ሥጋና ደሙን ለመቀበል የሚተጉባት፣ ከአባቶቹ ሕይወት በጎ ነገርን የተማረ ተረካቢ ትውልድ የሚተካባት፣ አንድ ወጥ አመራር የሚሰጥባት፣ ሰላምና ፍቅር የሰፍነባት፣ በተለያዩ ማህበራዊና መንፈሳዊ ችግሮች ውስጥ ያሉ ምዕመናን ከእግዚአብሔር ጋር የሚገናኙባት እውነተኛ የአምልኮት ማዕከል እንድትሆን ከተፈለገ በበሯ የምንገባና የምንወጣ ሁላችንም ዓይናችንን ከሰው ላይ አንስተን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንድንመለከት ያስፈልጋል። በተለይ ለልጆቻችን ስንል የቤተ ክርስቲያንን ጉዳይ በአደባባይ ላይ መዘርገፍና በአውደ ምኅረት ላይ መነቃቀፍን እርግፍ አድርገን ልንተው ይገባል። የሃይማኖት ጉዳይ በፍቅር እንጅ የፖለቲካን መስመር ተከትሎ በአመጽ የሚስተካከል አይደለምና። ለዚህም ቁልፉ በምዕመናን እጅ ነው። ከላይ የተጠቆሙትን የመፍትሔ ሐሳቦች ተጠቅሞ የጋራ ድካማችንን በምክክር ማስወገድና ለቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መከበር በአንድነት መቆም ያስፈልጋል። ካህናትና ምዕመናን እንደ ወይኑና እንደ ምሰሶው እንደጋገፍ እንጅ አንጠላለፍ። መደጋግፍ ሁለቱንም አካላት ባለክብር፣ ባለፍሬና፣ ባለዋጋ ያደርጋል። መጠላለፍ ግን ቤተ ክርስቲያንን ለውድቀት ይዳርጋል፣ መዘባበቻም ያደርጋል።
የቤተ ክርስቲያን አምላክ ሰሚ ጀሮ አስተዋይ አእምሮ ያድለን፤ አሜን።
ቀሲስ ዘመነ አቡሐይ

No comments:
Post a Comment