በልጅነቱ ገና በእምቡልቃ
አድጎ ተመድጎ ሳያበቃ
ክንዱ ሳይጠነክር ጉልበቱ ሳይጠረቃ
የቀለም አባቱን አጅቦ የኔታን ተከትሎ
አጎዛ ለብሶ ደበሎ ኮፌዳውን አንጠልጥሎ
በይ ደህና ሁኝ እናቴ
ለቤተ ክርስቲያኔ ለሃይማኖቴ
ዙሬ ተምሬ በሰው ሀገር እናንተን ላገለግል በእውቀቴ
ይኸው መሄዴ ነው ትምህርት ቤት መውጣቴ ነው ከቤቴ
ብሎ ተሰናብቶኝ ሲወጣ
አካሌ ቅድድ አለ ነፍሴ በአናቴ ወጣ
አልመሰለኝም ነበር ተመለሶ የሚመጣ
ከዚያች ዕለትና ከዚያች ሰዓት ጀምሮ
አእምሮየ በሐሳብ ተወጥሮ
ልቤ ከእሱ ጋር እንደ ዞረ ዓይኔ እንቅልፍ አጥቶ ስጨነቅ
ሞቷል ከእንግዲህ ብየ መርዶየን ስጠባበቅ
አንድ ተማሪ አየሁ አንድ ቀን
ራሱን ጠምጥሞ በሻሽ ቆሞ ሲለመን ከደጄ
እኔም ልዘከር ስወጣ እንጀራ ይዠ በቀኝ እጄ
እንጀራውን ተቀብሎ እንባና ሳቅ ተናነቀው
እኔም ግራ ግብት አለኝ
እንዴት አባቴ ልሁን እንዴት አድርጌስ ልወቀው
ልክ በሰባት ዓመቱ
ለካስ ልጀ ነው እሱ አድጎ ተመድጎ አንደ አባቱ
እኔ እኮ ነኝ እማየ ብሎ ሲስመኝ ጉልበቴን
ድንጋጤው ከልቤ ገብቶ አብረከረከው ሰውነቴን
ፍዝዝ ብየ ለደቂቃ ትንሽ ቆየሁና ቆሜ
በግንባሬ ተደፍቸ መሬቱን ዝቅ ብየ ስሜ
እልልልል…አልኩኝ ድንገት አንገቱ ላይ ተጠምጥሜ
ዓይን ለዓይን እየተያየን
ከበሩ ቆመን ለሁለት ስንላቀስ ብዙ ቆየን
ከዚያም ተያይዘን ወደ ቤታችን ገባን
ሁለታችንም እያነባን
ቁጭ እንዳልን ትንሽ ቆይተን
መጨዋወት ስንጀምር ተረጋግተን
ራሱን በእጁ ደገፍ አርጎ አንገቱን ወደ ቀኝ አዘንብሎ
አሳዛኝ ሕይወቱን ነገረኝ አጫወተኝ እንዲህ ብሎ
ምንም ትንሽ ልጅ ብሆን ለጋ ሰውነቴ ያልበረታ
ለተቀደሰ ዓላማ አሰልፎ ሁሉን አስቻለኝ ጌታ
የቆሎ ትምህርት መማር እየቆረጠሙ ቆሎ
ጎጆ ቀልሶ መኖር ቡቲቶ ለብሶ ደበሎ
የሻገተ እንጀራ እየበሉ ብስል ከጥሬ ቀላቅሎ
እየባነኑ ማደር እንቅልፍ አጥቶ በየዕለቱ
የወገን የሰፈር ትዝታው የቤተሰብ ናፍቆቱ
ከውሻ ጋር መታገሉ ሰፈር ለሰፈር መንከራተቱ
ለቁራሽ እንጀራ ቆሞ በሰው ዓይን መገመቱ
ስንቱ ተወርቶ እማየ እረ ስንቱ እረ ስንቱ
አንዲህ እያለ ልጄ ታሪኩን ሲነገረኝ በጽሞና
ከአባቱ ቤት ሁሉ ተርፎ ሰባት ዓመት በልመና
ያሳለፈውን ሕይወት ስሰማ የገጠመውንም ፈተና
ሆዴ አልችል አለኝና እንባየ መጣኝ እንደገና
አስተዳደጉን እያስታወስኩ ምንም ቢከፋው ሆዴን
የነፍሴ እረኛ ሆነ ልጄ ሊያስተካክልልኝ መንገዴን
ቀሰሰና በሥርዓቱ አብረን መኖር ጀመርን
እያመሰገንን እግዚአብሔርን
ከፍ ያለ ማዕርግ ሲሰጠው
ለቅስና ሲበቃ መልካም ነገር አዩ ዓይኖቸ
እኔም አንቱ አልኩት ልጀን አንተ ማለቱን ትቸ
በጣም ደስ አለው ልቤን ኮራሁ በልጄ እኔ እናቱ
በአገልግሎት ላይ ተሰማራ ረካች ነፍሴ በትምህርቱ
ነገር ግን መቸ ይሆን እፎይ የሚለው እሱ
ዛሬም አልወረደም ገና የመከራው ቀንበር ከራሱ
ያ ሁሉ ደጅ ጥናት እግርን በውሻ መበላቱ
ለመነቀፍ ለመዋረድ ለካስ ይኸው ነው ሽልማቱ
በየዕለቱ መሮጡ ጦሙን ማደሩ ሳያንሰው
አሁንም ተማሪ ነው አባ ትምህርቱን መች ጨረሰው
ሲሞት ብቻ ነው አሱ የነፍሴ እረኛ የሚያርፈው
ላይከብርበት በሥጋው ምንም ነገር ላይተርፈው
ይኸው ዛሬም አይታክትም
የሰው ውሻ ሲጮህበት የምላስ ጅራፍ ሲገርፈው
ሰሙ በሜዳ ይዘራል ያለበደሉ ይከሰሳል
እያገለገለ ይወቀሳል
እንደ ውሃ ፍልቶ ይበርዳል ሳይውድ በግድ ይታገሳል
እንደ ሻማ እየቀለጠ የጥበብ ብርሃኑን ይለግሳል
እያለቀሰ ያስለቅሳል ቁስለኞችን ይፈውሳል
አቅሜ ባይፈቅድልኝም አንኳን ምንም ባላግዘው በጥቂቱ
ከቤተ ክርስቲያን ጓሮ ቆሜ በየዕለቱ
እጸልይለታለሁ እኔ እናቱ
እሱም ቢሆን ጠንካራ ነው እጅግ በጣም የሚያኮራ
የክህነት አገልግሎት ምንም ሲሆንበት መራራ
የመምህሩን ቃል ኪዳን የፈጣሪውን አደራ
ሸክም ሲብደው አንድ ቀን ይጥለዋል ብየ ስፈራ
ሊጥለው አይፈልግም ይነገዳገዳል ያለአቅሙ
ለካስ ለክብር ነው እርሱ የግፍ ቀንበር መሸከሙ
ይህን እያወቅሁ እኔ ለቆመለኝ ለነፍስ አባቴ
ላግዘው ሲገባኝ በጸሎቴ
ክፉ ብናገር ስለእርሱ ትከሰኝ አለች ነፍሴ
ሞት እንደሆን አይቀርም ነገ ይታሠራል ምላሴ
ጠንቃቃ ሐኪም ነው ብልህ ዳኛ
የማይታክት የማይተኛ
የገነት ቁልፍ በእጁ ያለ የመንገሥተ ሰማያት በረኛ
አባ የነፍሴ እረኛ