የልዑል አምላክ እንደራሴ ስሙ ከፍ ብሎ የሚጠራ
በሕዝብ አእምሮ ውስጥ ዘልቆ እንደ ኮከብ የሚያበራ
አእላፍ ነፍሳትን እንዲታደግ የተሰጠው አደራ
በተሰለፈበት ኪነ-ጥበብ በልዩ ሙያው የታወቀ
ሥልጣን ከአርያም የተሰጠው ስለታማ ሰይፍ የታጠቀ
በፈውስ ሙያ የተካነ በቃለ አስተምህሮ የረቀቀ
ጤና ያጣ የነፍስ ሐኪም መጎዳቱን ያላወቀ
ራስ ወዳድነት አሸንፎት የገባውን ቃል በማፍርሱ
የሞያ አቅጣጫው የጠፋበት የታወከበት መንፈሱ
በነዋይ ልክፍት በዘር በሽታ እየተሰቃየች ነፍሱ
የቀመመውን መድኃኒት መጠቀም ተስኖት ለራሱ
መቆም አቅቶት ሲንገዳገድ እንዴት ያሳዝናል እሱ!!
ሃይማኖታዊያን ደንበኞቹ የነፍስ ደዌ ያጠቃቸው
ምንም ሐኪሙን ባያምኑት መታመሙ ቢገባቸው
የቀመመውን መድኃኒት ሊጠቀሙበት ለራሳቸው
ለነፍሳቸው ታዳጊ እየጸለዩለት በልባቸው
አልቀረም በተለምዶ ይፍቱኝ አባቴ ማለታቸው
ጤና የጎደለው የነፍስ ሐኪም ሐኪሞችን የሚዋጋ
የዘር ኃረግ እየሳባ ከቆላና ከደጋ
ምርቃትንና እርግማንን እያስተናገደ በጸጋ
በመዘዘው የክፋት ሰይፍ የመለያየት አዳጋ
ሰላምን የሚያጭልም የድኅትን በር የሚዘጋ
ተስፈኞችን የሚጎዳ በነፍስም ሆነ በሥጋ
እንዳያስተምሩት ምሁር እንዳይመክሩት መካሪ
ለማን ይገባል ልመና ይቅር እንዲለው ፈጣሪ
እንደ አመጸኛ ካህን ለሰው ለእግዚአብሔር አስቸጋሪ
በባከኑት ነፍሳት ቁጥር የእንባ ዘለላ ሠርቶ
ያስለቀሳቸውን እንዲክስ በክፉ ሥራው ተጸጽቶ
የንስሐን በር እንዲከፍት አርአያነቱን አሳይቶ
ይቅር እንዲለው ፈጣሪ ሰው መሆኑን ተመልክቶ
በፍቅር ሆኖ ለዚህ ሰው መጸለይ ይገባል አብዝቶ
ቀሲስ ዘመነ አቡሐይ
ሳን ሆዜ ካሊፎርንያ