HOME FOR SPIRITUAL MESSAGE BY FR ZEMENE DESTA

ልጅ ለእናቱ

ከሞት አዋጅ ለመታደግ ከተደቀነባት አዳጋ
ተዋሕዶ ልጆቿን አሰባስባ በጉያዋ ሸሽጋ
እየተንገላታች በስደት በቆላና በደጋ        
በድኅነት አቅሟ በማር በወተት አሳድጋ
ዛሬ ሊያልፍላት ሲቃረብ ጨለማው አልፎ ሲነጋጋ

የልጅ ጠላት ተንስቶባት
የጥፋት ሰይፍ መዞባት
እናት ከልቧ አዘነች፣
የወላድ መካን ሆንኩ አለች

አንተ ዘመናዊ  አማኝ መሳይ በዴማስ ጎዳና የምትሄድ
ስለ ተሳነህ መከተል የእግዚአብሔርን በጎ ፈቃድ
ብታመለክትህ እምየ የአባቶችህን መልካም መንገድ
ፊትህን አዙረህ ሸምቀሃል ወላጅ እናትህን ለማሳደድ
መታዘዝን ያልመደ ልብህ ተመኝቷል አሉ ዘንድሮ
ተዋሕዶን ገፍትሮ አሽቀንጥሮ
በአዲስ እምነት ቀይሮ
ሰፊ ጎዳና ልቅ ሥርዓት ዘመናዊ ሕይወት ምቹ ኑሮ

ተው ረጋ በል ወዳጀ አስተውል እንጅ አትሳሳት
የሚያብለጨልጭ ሁሉ ወርቅ እንዳልሆነ ተመልከት
ይህችን አሮጊት እናትህን አትናቃት ልጄ አደራ፣
በፍቅር መኖር ብትችል ጠጋ ብለህ ከእርሷ ጋራ፣
እውቀት ልምዷን ብትሸምት እንደ አባቶችህ ብትሠራ፣
ያካበተችው ሐብት ብዙ ነው ትውልድ ሀገርን የሚያኮራ፣

የምሥራቅ አፍሪካ ፀሐይ የምትፍለቀለቅ ደምቃ
ከአውሮፓውያን አስቀድሞ በመንፈሳዊ ጥበብ ልቃ
በሥነ-ቋንቋ በልጽጋ በዘመን ቀመር ተራቃ
ፊደል ቀርጻ ብራና ፍቃ
ጽፋ ደጉሳ ጠንቅቃ
በእሳት በስለት ተፈትና ታሪክ ባሕልህን ጠብቃ
ያኮራችህን እናት አንተን ከዓለም ጋር አስተዋውቃ
ምን ተገኘባት እኮ ዛሬ ለመነቀፍ የሚያበቃ
ደጋፊ ልጆቿን አጥታ እንድትሰባበር ወድቃ
ሐሳዌ መሲህ ብቻ ነው እሷን ለይቶ የሚያጠቃ

ሐሳዌ መሲህ ፓስተር ውሎህ ከማን ጋር ነበረ
በክህደት ጎዳና ከነፈ እንጅ እንዲሁ ወጥቶ በረረ
የጥበባትን መዝገብ ሊመረምር ልቡናህ መች ደፈረ
ጥበብ እሱ ነው የጥበብ ምንጭ በተዋሕዶ የከበረ
ሁሉን ይዞ የድኸየ ጦም ውሎ ጦም ያድረ
ጽድቅ በሥራ መሆኑን ያስተማረ
ገድማዊ ሕይወትን የጀመረ
ለቅዱሳን መታመንን የአምላክነት ጸጋን የቸረ
የመለያየትን ግድግዳ በጥብቡ ያፈረሰ
በሥጋውና በደሙ ዓለምን የቀደሰ 

ካልተሰበሩ በትህትና ካልደከሙ በሥጋ
ጥበብ ከጎዳና አይገኝም ያለድካም ያለ ዋጋ
መጽሐፍ ቅዱስን እያነበብክ በማስተዋልና በጸጋ
የቀደመትን ትውልድ ጠይቅ ለአባቶችህ ጥበብ ትጋ
(ኢዮ 8፡8)

ካዳመጥከኝ ላስታውስህ ከተጻፈው በጥቂቱ
ይህ አይቀርም የግድ ነው ይፈጸም ዘንድ ትንቢቱ
የፍጻሜው ዘመን ሲደርስ ሰይጣን ሲፈታ ከእስራቱ
ቅዱሳንን ሊዋጋ አውሬው አፉን መክፈቱ
መቅበዝበዙ መወራጨቱ ማታለሉ ማምታታቱ

በሕገ ተቃውሞ የሚመራ የሰለጠነብህ እኩይ መንፈስ
ምግባር ትሩፋትን አስጥሎ ቤተ መቅድስን የሚያፈርስ
ቋንቋ ፍጥሮ የሚያናግር ያልታመሙትን የሚፈውስ
መጽሐፍ ቅዱስን ጠምዝዞ በልብ ወልድ በፈጠራ
ልጅ አባቱን እንዲረግም  እግዚአብሔር እንዳይፈራ
ጾምን በመብል ቀይሮ ማህሌትንም በጭፈራ
ለቃሉ የማይታዘዙትን ትውልደ አራዊተ ገሞራ
ልባቸውን አጨልሞ ወደ ጥፋት የሚመራ
ተማምሏል በቃል ኪዳን እሱ መንፍስ ከአንተ ጋራ

የመውጊያውን ጦር ብትቃወም ይብስብሐል ለአንተ
ከተረገመ ይሻላል የተቀበረ የሞተ
እማማን ንቀህ አቃለህ
ታሪካዊ ውርስህን ጥለህ
በጥራዝ ነጠቅ ቆነጣጥረህ የምዕራባውያንን ፍልስፍና፣
ልትረጋግጣት በትሞክር ተዋሕዶን በጎዳና፣
ፍለጋዋን አታገኝም መንገድህ ግራ ነውና፣
በቅዱሳን ጸሎት ይበናል መንፍስህ በደመና
የአምልኮት ሥርዓቷ ሳይጓደል መሠረቷ እንደጸና፣
የጽድቅ በሯ ሳይዘጋ በእግዚአብሔር መንግሥት ተከውና
ታማኝ ልጆቿን አሰባስባ ያለፉትን በፈተና
ተዋሕዶ እናታችን ትኖራለች ተሽሞንሙና፣
እድሜዋ ረዘመ እንጂ መች አረጀችና እሷ ገና፣

ውለታህን የረሳህ  አንተ ክፉ የክህደት ስው
ሁከት የሚዘራ ደረቅ ቃልህ ስንቱ እንደ ውሻ አናከሰው 
ሙት ብየ በአንተ አልፈርድም አምላክ ልብህን ይመልሰው
………………………………………………………………………………………………

ደግሞ አንተኛው ኦርቶዶክሳዊ እግርህ ከቤት ሳይወጣ
የወንድምህ የአመጽ መንፈስ በየት አልፎ ከአንተ መጣ
በማይታጠፍ ቃል ኪዳን በእምነትና በተስፋ
የታሪክ ወራሽ ልትሆን ተዋሕዶን ልታስፋፋ
የአባቶችህ አደራ ለአንተ አልነበር የተሰጠ!
ሙገሳው በዛብህ እንዴ ምነው ጸባይህ ተለወጠ!!

ተው ወዳጄ ይቅርብህ!!
ምክረ አበውን አታቃልል ለታሪክህ ዋጋ ስጥ
በሊቃውንት ፊት አትፈንጭ በአባቶችህ ላይ አታላግጥ          
ቃሉን በልባቸው ያውቁታል አንተ መጽሐፉን ሳትገልጥ

የተዋሕዶን ምሥጢር መርምር የሕዝብህን ታሪክህ አጥና፤
የአባቶቻችን መታወቂያ ፍቅር አንድነት ነው ትኅትና
በጸሎት ኃይል ካልተገፈፈ የተዋሕደን ስንፍና
በቃሉ አድገን ካልተለወጥ ን ታዲያ ምንድር ነው ክርስትና!

በደለኛው ተጸጽቶ ካላነባ ለራሱ
አንደበቱ ካልተገራ ካልተሰበረ መንፈሱ
ከመንፈሳዊ ምግብ ካልተሻማ ለተራበችው ነፍሱ
ታዲያ የት አለ ፍሬው የወንጌል ትምሕርት አዝመራ
ካልተገለጠ  በሥራ ካልሙላ በጎታራ
እኮ የት አለ ምርቱ!!
የሚዘራው የእግዚአብሔር ቃል የምንሰማው በየዕለቱ

መንፈሳዊነት ውሉን አጣ መጠላለፉ መጣም በዛ!
ለጀሮም ሰለቸ ጠነዛ ፡፡        

ከአሮን ድንኳን ስትገባ ወደ እግዚአብሔር ቤት ስትመጣ፣
አንደበትህን ሰብስብ አድርግ ከአባቶህ ቃል አትውጣ
ፈጥነህ ጣትህን አትቀስር በወንድምህም ላይ አትቆጣ

ራስህን አዘጋጅ ለመማር እኔ እውቃለሁ አትበል፣
በፈሪሃ እግዚአብሔር ተመላለስ በትዕግስትና በማስተዋል  
እንደ ይስሃቅ በመታዘዝ በረከትን ለመቀበል፤
ከአድመኞች ሸንጎ ራቅ ከይሁዳ ሸፍጥ ከተነኮል

የእኔ የአንተ እናት ተዋሕዶ የማይገኝላት አቻ
የፖለቲከኞች ዱላ ሳይበግራት የመናፍቃን ጥላቻ
በእኔና በአንተ ሽኩቻ
መተቻ ሆነች መተረቻ

ቅን አሳቢ ጠፋና እግዚአብሔርን የሚፈራ፣
ለይስሙላ ተሰብስበን በተቀደሰው ተራራ፣
በዘር በፖለቲካ ተጠምቀን ልባችን በቃሉ ሳይገራ
የምቀኝነትን ወንጌል ስንሰብክ አሉባልታ ስናወራ፣
ከመናፍቃን ቤት ገባ ፍቅር ተሰዶ በተራ፣
የተዘራው ዘር ተንሰራፋ አድጎ በሰለ ጎመራ፣
አለመተማመን ወለደ ጥርጣሬን አፈራ፡፡

ምነው አከራካሪ ሆነ የተዋሕዶ ልጆች የእምነት ጎዞ
ቃኤል በግራ እጁ ሰይፍ ይዞ አቤል በውስጡ ሞት አርግዞ
በራሷ ልጆች ተፈትና መረጋጋትን አጥታ 
ክፉኛ አዘነች እማማ  ተማለለች ወደ ጌታ
ቃሏን ከፍ አድርጋ አሰምታ፣

ስለዚህ ወዳጀ ስማ!!
ጅምርህ እንዲጸና መሠረትህም እንዲስፋፋ
አበባ ሁነህ እንዳትቀር ዛሬ ታይቶ የሚጠፋ
እውን እንዲሆን ሕልምህ የምትጠብቀው በተስፋ
አረማመድህ ይመር ልብህ ይጽና በተአምኖ
ያስፈልግሀል አባት የሚመክርህን ከጎን ሆኖ

ሰላም ሆነህ ሰላም ስጣት ለተዋሕዶ እናትህ ለአንዲቱ፣
ደጋፊ እንጂ ምርኩዝ ያዥ ቅንቅን አይሆንም ልጅ ለእናቱ
አረማመድህን አስተካክል ራስህን መዝን በየዕለቱ
ዋጋ ቢስ ሆኖ እንዳይቀር አገልግሎትህ በከንቱ

ብንመካከር በፍቅር ተቀራርበን ሁላችን፣
ውበቷ ደምቆ ይበራል ደስ ይላታል እናታችን
እኛም እንኮራለን ሁላችን፣ እሷ ናትና ውበታችን
ስማችን ይታደሰላ በወርቅ ይሠራል ቤታችን

ስለዚህ ወዳጀ ስማ!!
ሰላም ሆነህ ሰላም ስጣት ለተዋሕዶ እናትህ ለአንዲቱ፣
ደጋፊ እንጂ ውለታ መላሽ ቅንቅን አይሆንም ልጅ ለእናቱ


ቀሲስ ዘመነ አቡሐይ
ሳን ሆዜ  ካሊፎርንያ