ሰው በስደት ሲኖር ከሀገሩ ርቆ
የሀገሩ ወኪል እንደሆነ አውቆ
ለሚሠራው ሥራ በጣም ተጠንቅቆ
የሃይማኖቱን ሕግ እንደ ዝናር ታጥቆ
የዜግነት ክብሩን ባሕሉን ጠብቆ
ልጅ ለአባቱ ታዞ እንደ ልጅነቱ
ሽማግሌው ታፍሮ በአረጋዊነቱ
ተከባብሮ መኖር ሁሉም እንደ እምነቱ
ይህ ነው የጭዋ ደንብ ወግና ሥርጫቱ
የእምነት ማዕከላችን ያለች የነበረች
እንከን የሌላት ወርቅ ከአልማዝ የከበረች
ዜጎች በጭንቅ ቀን የሚጠለሉባት
እኛው ራሳችን ብንሆንባት ጠላት
እርሷን መራቅ ጤና ተብሎ ስም ወጣላት
ቢዝነስ ተኮር ስብከት በውል የተጠና
የመድረክ እሽቅድድም ለታይታ ለዝና
ለሰላም ካልበጀ ለሕዝቦች አንድነት
ቂም በቀል ያዘለ ሥርዓተ አምልኮት
የዝማሬ ብዛት የማህሌት ድምቀት
ኪሳራ ነው ትርፉ የድካሙ ውጤት
ሳይገባን ምሥጢሩ የሃይማኖታችን
በልማድ ሆነና መሰባሰባችን
ተመቸው ዘንድሮ ሰይጣን ጠላታችን
መቅድስ ዘልቆ ገባ መዘነው ልባችን
ዜጋ ስሙ ገኖ የሚጠራው በዓለም
በበጎነት እንጅ በሁከት አይደለም
በስደትም ስንኖር ከሀገር ርቀን
ይበጀናል መኖር ስማችን ጠብቀን
አንቀርም በስደት በሰው አገር ወድቀን
እንመለሳለን ሁላችን አንድ ቀን
ባለታሪኮች ነን ዓለም ያደነቀን
ቃል ኪዳን እንግባ...፤
በዘር መለያየት ሊቀር አሉባልታ
ለዜግነታችን ልንሰጠው ቦታ
ቃል ኪዳን እንግባ ልባችን ይረታ
ኢትዮጵያውያን ሁሉ እንደ ባሕላችን
ተከባብረን ልንኖር በአንድነት ሁላችን
የምንገናኝባት የእምነት ማዕከላችን
ትንሽዋ ኢትዮጵያ ልትሆን የጋራችን
ታሪክ ተለውጦ ሊታደስ ስማችን
ቃል ኪዳን እንግባ እኛው ለራሳችን
ቀሲስ ዘመነ አቡሐይ
ሳን ሆዜ ካሊፎርንያ