HOME FOR SPIRITUAL MESSAGE BY FR ZEMENE DESTA

መድበለ - ግጥም

“ሁለትን ነገር ከአንተ እሻለሁ፥ ሳልሞትም አትከልክለኝ፤ ከንቱነትንና ሐሰተኛነትን ከእኔ አርቃቸው፤ ድኅነትንና ባለጠግነትን አትስጠኝ፤ ነገር ግን የሚያስፈልገኝን እንጀራ ስጠኝ፥ እንዳልጠግብ እንዳልክድህም። እግዚአብሔርስ ማን ነው? እንዳልል፤ ድሀም እንዳልሆን እንዳልሰርቅም፥ በአምላኬም ስም በሐሰት እንዳልምል” (ምሳ 30፡8)።
...................................................................................................
·        የነፍሴ እረኛ
·        ታማኝ ሁን አደራ
·        ልጅ ለእናቱ 
...................................................................................................


በሒሶጵ እርጨኝ
የነፍሴ መጋቢ ቅን እረኛ ተነግሮ የማያልቅ ቸርነትህ
ዝመታህ ያስፈራኛል ስመላለስ በፊትህ
ደካማነቴን አይተህ አስበኝ በምረትህ
የሚዋልለው ስሜቴ መንፈሴ ተረጋግቶ
                     ልቡናየ ልብ ገዝቶ
ቃልህን እንዲያዳምጥ ዕዝነ ኅሊናዬ ተከፍቶ
የክርስትና ትርጉም ሳይገባኝ በስሜቴ ተገፍቸ
በማይገባኝ ቦታ ቆሜ ያለሥራዬ ገብቸ
የሰው ገመና መዘርዘር መክሰስ መኮነን ተቸ
ለራሴ እንዳለቅስ ተጸጽቸ

ሞገስ ሆኖልኝ ክርስትና ስምህን እንደ ጋቢ ለብሸ
በቅብአ ሜሮን ታትሜ እንዳልታይ ቆሽሸ
በእኔ ኃጢአት በእኔ ሥራ
ስምህ በከንቱ እንዳይጠራ
የዜግነት ክብሬ እንዳይጎድፍ እንተ እንዳትነቀፍ በተራ
የሚያሳድዱኝን ሰዎች ስም በጥላቻ እንዳላነሳ
ሁሉን ነገር ለአንተ ትቸ ቂም በቀልን እንድረሳ
ቀናውን መንፈስ ስጠኝ ጌታ
ልቤን ክፈተው ለይቅርታ
በከበረው ደምህ እጠበኝ በሂሶጵ እርጨኝ በጠብታ

ሥጋዊ ሐሳብ አሸንፎኝ መሪ ቃልህን ተላልፌ
ሰው እያየሁ ስደናበር እንዳልወድቅ ተደናቅፌ
እንዳገለግልህ ወደ ፊት መሰናክሉን አልፌ
ምርኩዝ ስጠኝ ለቀኝ እጄ የምመራበት ተደግፌ

ክፈትልኝና ዓይኔ ይብራ
የኃጢአቴን ግዝፈት ተመልክቸ
            ክፉ አንደበቴ እንዲገራ
እለምንህ አለሁ አባት ሁሉም ከአንተ ነውና
ከጥበባት ጥቂቶቹን እንድትሰጠኝ በልግስና
በፍቅር የታነጸ እመነት የይቅርታ መንፈስ የትህትና
የሰማውን ሁሉ የሚሸከም ትዕግስት የተሞላ ልቡና

ኃጢአተኛነቴን ተረድቸ ማንነቴን አውቄ
በሥጋ ደምህ እንድከብር በንስሐ ተጠምቄ
ቅድስናንና ለብሸ ስምህን እንደ ዝናር ታጥቄ
ሐሰት ከመናገር ርቄ
እንዳገለግልህ ተጠንቅቄ

ቀናውን መንፈስ ስጠኝ ጌታ
በከበረው ደምህ እጠበኝ
            በሂሶጵ እርጨኝ በጠብታ

ቀሲስ ዘመነ አቡሐይ
ሳን ሆዜ ካሊፎርንያ