የዚህ ድኅረ ገጽ ዋና ዓላማ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ቀጥተኛ አስተምሕሮ፣ (ዶግማና ቀኖና) ለቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች ማስተማር፣ እውነተኛውን የቤተ ክርስቲያን ትውፊትና ያልተበረዘ ሥርዓት ከሰው ሠራሽ ልማድ ለይተው እንዲያውቁ ማገዝ፣ በወጣቱ አእምሮ ውስጥ የሚመላለሱ መንፈሳዊና ሃይማኖታዊ ጥያቄዎችን ማስተናገድ፣ እንዲሁም መንፈሳዊ፣ ማህበራዊና ሥነ-ልቡናዊ ችግር ለገጠማቸው ኦርቶዶክሳዊያን የምክር አገልግሎት መስጠት ነው።
የሰው ልጅ በተፈጥሮ ምሉዕ የሆነ የእውቀት ጸጋ ከአምላክ ዘንድ የተቸረው ልዩ ፍጥረት ቢሆንም ጥበብንና ዕውቀትን በአንድ ሌሊት እንደ ባትሪ ሊሞላ (ቻርጅ ሊደረግ) የሚችል መሣሪያ አይደለም። ስንወለድ ተፈላጊውን የጥበብ ዘርፍ ሁሉ ደረጃ በደረጃ ሊቀበል የሚችል ባዶ አእምሮ ንጹሕ ሰሌዳ (ታቡላራዛ) ይዘን ነው ወደዚህ ዓለም የምንመጣው። ስለዚህም ግለሰቡ ከሚፈልገው የዕውቀት ደረጃ ለመድረስ መማር፣ መጠየቅና ማንበብ ይጠበቅበታል። በተለይ የሃይማኖት ጉዳይ ልዩ ጥንቃቄን የሚጠይቅ በመሆኑ ወጣቱ ትውልድ ስለ ቤተ ክርስቲያን ዶግማ፣ ቀኖናና ሥርዓት በመሰለኝ ከማናገሩና ለሌላው የምስክርነት ቃሉን ከማስተላለፉ በፊት የቤተ ክርስቲያናችንን ትምህርት በመደበኛነት ከተማሩ አገልጋዮች ቢጠይቅና ቢያረጋግጥ የተሻለ ይሆናል። ይህን በማድረጉ የሌላውን አእምሮ ሊገነባ የሚችል ትክክለኛና ያልተዛባ የምስክርነት ቃለ ለማስተላለፍ ዕድል ስለ ሚኖረው በሥጋ የአእምሮ እርካታና የነጻነት ስሜት፣ በመንፈስ ደግሞ ሰማያዊ በረከትን ያገኛል። አስቀድሞ “ዘመናችን በምድር ላይ እንደ ጥላ ነውና እኛ የትናንት ብቻ ነን፤ ምንም አናውቅም፤ ስለዚህ የቀደመውን ትውልድ ጠይቅ፥ አባቶቻቸውም ለመረመሩት ነገር ትጋ፤ እነርሱ የሚያስተምሩህና የሚነግሩህ፥ ቃልንም ከልባቸው የሚያወጡ አይደሉምን? በውኑ ደንገል ረግረግ በሌለበት መሬት ይበቅላልን? ወይስ ቄጠማ ውኃ በሌለበት ቦታ ይለመልማልን?” (ኢዮ 8፡8) ተብሎ ተጽፏልና።